Skip to main content

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ለገጠር ቀበሌ ስራ አስኪያጆች ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ለገጠር ቀበሌ ስራ አስኪያጆች ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ።

ሳጃ፣ ታህሳስ 7/2017 ዓ/ም

አካዳሚው ከክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር "የመልካም አስተዳደር እምርታ በቀበሌ" በሚል መሪ ቃል ከክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የተመረጡ የገጠር ቀበሌ ስራ አስኪያጆች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን አስታውቋል።ስልጠናው ከታህሳስ 9 እስከ 11/2017 ድረስ በሆሳዕና ከተማ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ እንደሚሰጥም አካዳሚው ገልጿል።

ይህንኑ አስመልክቶ የክልሉ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።የስልጠናው ተሳታፊዎች በክልሉ ከሚገኙ የተመረጡ 702 ቀበሌያት የተውጣጡ ስራ አስኪያጆች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በአገልጋይ መሪነት እንዲሁም በመረጃ አያያዝና ማዘመን ላይ የሚያተኩር ስልጠና ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በስልጠናው የቀበሌ ስራ አስኪያጆችን በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በማድረግ በሀገር ግንባታ ሂደት የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል።ስልጠናው መነቃቃት በመፍጠር ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ስለመሆኑም አክለው ገልፀዋል።በክልሉ አካዳሚው ባከናወናቸው የጥናት ስራዎች የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መኖራቸውን መለየት መቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል።ከህብረተሰቡ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የቀበሌ ስራ አስኪያጆች የመንግሥት የልማት ግቦችንና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን እውን ለማድረግና እምርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ሚናቸው ጉልህ መሆኑን ገልፀዋል።

የስልጠናው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ ሰልጣኞች ነገ ታህሳስ 8/2017 ከቀኑ 8 ሰዓት በፊት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እንዲገኙም አሳስበዋል።

Image
photo