Skip to main content

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ቀበሌያት መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ እና የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለቀበሌ ስራ አስኪያጆች እየተሰጠ ነው።

የቀበሌ ስራ አስኪያጆች በገጠር ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት መወጣት አለባቸው፦ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ

ሳጃ፦ታህሳስ 9/2017ዓ.ም

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ቀበሌያት መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ እና የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለቀበሌ ስራ አስኪያጆች እየተሰጠ ነው።

ስልጠናውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ አመራር አካዳሚ ከክልሉ ፐቭሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።"የመልካም አስተዳደር ዕምርታ በቀበሌ"በሚል መሪ ቃል ስልጠናው ለሶስት ተከታታይ ቀናት እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው መክፈቻ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካትና የተሟላ ብልጽግና ለማረጋገጥ የቀበሌ ስራ አስኪያጆች ሚና ከፍተኛ ነው።የቀበሌ ስራ አስኪያጆች በተሟላ ደረጃ በመንቀሳቀስና የሚለካና የሚጨበጥ ዕቅድ በማቀድ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በላቀ ደረጃ ማገዝ እንዳለባቸው ዶክተር ዲላሞ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የህዝብ እንቅስቃሴን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑንም አመላክተው ከአንዱ ስራ ወደሌላ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሸጋገርን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል።የቀበሌ ስራ አስኪያጆች ሌላው ማተኮር ያለባቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ማስፋፋት ፣ቀበሌን ከቀበሌ የማገናኘት፣የውሃ የመብራት የመንገድ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በማስፋፋት ላይ እንዲሆንም ዶክተር ዲላሞ አሳስበዋል።ስራ አስኪያጆቹ የማህበረሰብ ባህላዊ ለውጥ እውን እንዲሆን ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑንም አመልክተው በአመት ሶስት ጊዜ ማምረት፣ በአመጋገብ፣ በአነጋገር፣ በአስተሳሰብ፣በአኗኗርና በመሳሰሉት ዘርፎች መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።

እነዚህ መሰረታዊ ለውጦች እንዲመጡ በመጀመሪያ የቀበሌ አመራሩ አቅምና አመለካከት መጎልበት እንዳለበትም ዶክተር ዲላሞ ጠቁመው የዛሬው ስልጠናም የዚህ አካል እንደሆነም አስረድተዋል።አገልጋይ መሪ መሆን፣መሪው ሌሎችን ለውጦ የሚያልፍ መሆኑን መረዳት እና ቀበሌን አንድ ደረጃ ለማሻገር አቅዶ መረባረብ ተገቢ መሆኑንም አስገንዝበዋል።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቦችን ለመለወጥ የቀበሌ ስራ አስኪያጆች ያላችሁ ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ በተሻለ መነሳሳት ስልጠናውን መውሰድና ለተግባራዊነቱ መዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነም ዶክተር ዲላሞ መልዕክት አስተላልፈዋል።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ ስልጠናው በገጠር ቀበሌያት መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በቀበሌ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት ብልጽግናን በየደረጃው ለማረጋገጥ መሰል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የአመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላቱ በበኩላቸው አካዳሚው የተሰጠውን ችግር ፈቺ ተግባራዊ የምርምር ስራዎችን የማረጋገጥና ለአመራሩና ለፈጻሚዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን አጠናክሮ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።ለቀበሌ ስራ አስኪያጆቹ እየተሰጠ ያለው ስልጠና የአገልጋይነት እሳቤዎችን ለማስረጽ፣መልካም አስተዳደርን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል፣የተሻለ ዕቅድ እንዴት ማዘጋጀትና መተግበር እንደሚቻልና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩርም አስረድተዋል።

ስልጠናው ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ ምሁራን እንደሚሰጥም አቶ ተስፋዬ አስታውቀው ሰልጣኞች ስልጠናውን በልዩ ትኩረት እንዲከታተሉም አሳስበዋል።

Image
photo