የበጎ ፍቃድ ተግባራት ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከርና የህብረተሰቡ የእርስ በርስ ግንኙነቶች በማሻሻል ረገድ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፦አቶ ተስፋዬ ብላቱ
ሀምሌ 23/2018 ዓ.ም(ሳጃ)
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ከክልሉ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በጉራጌ ዞን እምድብር ከተማ አስተዳደር የአንድ አረጋዊ ቤት ግንባታን አስጀመሩ።
በከተማዋ የተቋማቱ አመራሮችና ሰራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም አካሂደዋል።
የማእከላዊ ኢትዪጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላቱ እንደገለፁት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚከናወኑ የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች አንዱ የክረምት በጎ ፍቃድ ተግባር ተጠቃሽ ነው።
የበጎ ፍቃድ ተግባራት ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር፣ የህብረተሰቡ የእርስ በርስ ግንኙነቶችና ትውውቅ በማሻሻል ረገድ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ አካዳሚው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ዋና ዓላማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች መጠለያ ያጡና አረጋውያንን በመደገፍ ሰብአዊ አጋርነትን ማሳየት ሲሆን በዚህም በክረምቱ ወራት በርካታ አረጋውያን አዲስና የተሻለ መጠለያ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
የሀገር ባለውለታ የሆኑና አስተዋጽኦ ያበረከቱ ወገኖች የገጠማቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለማቃለል እየተከናወኑ የሚገኙ የክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በመሆኑም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ አቅመ ደካማ ለሆኑ ወገኖች ደረጃውን የጠበቀ ቤት የሚገነባበትና የሚታደስበት፣ የነገ ትውልድ የምንጠቅምበት ወሳኝ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ አካዳሚው ከክልሉ ወሳኝ ከነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በጉራጌ ዞን እምድብር ከተማ የተጀመረው የአንድ አረጋዊ ቤት ግንባታ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል።
አያይዘውም አቶ ተስፋዬ በበጎ ፍቃድ አማካይነት የሚተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርና የአየር ንብረት ለውጥ በመከላከል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ተገቢውን ክብካቤ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በክልሉ አስራ አራት አይነት የበጎ ፍቃድ ተግባራት በሁሉም አካባቢዎች እየትከናወኑ መሆኑን በመግለፅ ተግባራቱ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ወጣቶች የአረጋውያን ቤት በመገንባትና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቤተሰብ በመደገፍ፣ ደም በመለገስና በሌሎችም ዘርፎች ላይ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የክልሉ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ከሚተገበሩ ሰው ተኮር ስራዎች አንዱ የበጎ ፍቃድ ስራ ሲሆን ባለፉት አመታት የዜጎች ህይወት የሚቀይሩ፣ ዜጎች የአብሮነት፣ የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን ተላብሰው እንዲኖሩ የሚያስችሉ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
በበጎ ፍቃድ ተግባር ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ አቅመደካሞችን መርዳት ሲሆን ኤጀንሲው ከክልሉ አካዳሚ ጋር በመተባበር ደረጃውን የጠበቀ ቤት ለመገንባት ሙሉ የግንባታ ቁሳቁስ ማቅረብ እንደተቻለ ገልፀዋል።
በዚህ ሰው ተኮር ስራ የተቋማቱ አመራሮችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን ውጤታማነቱን እንዲረጋገጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በየደረጃው የተጀመሩ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው እንዱቀጥሉ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
በበጎ ፍቃድ ስራ በተከያዩ አካባቢዎች ለአቅመ ደካሞች ቤት በጥራትና በፍጥነት ገንብቶ የመጨረስ ልምድ ስላለን ዛሬ ግንባታው የተጀመረው የአረጋዊ ቤት ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የእምድብር ከተማ ከንቲባ አቶ ግንባሩ በርጋ የክልል ተቋማቱ እያደረጉት ያለው የበጎ ፍቃድ ተግባር የሚደነቅ እንደሆነ ገልፀዋል።
በተቋማቱ አማካይነት እየተገነባ የሚገኘው የአረጋውያን ቤት በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
አቶ አብሽሮ ቴኒ በበኩላቸው በክረምቱ ወራት በሚጥለው ዝናብና ቅዝቃዜ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥርባቸው እንደነበር ገልፀዋል።
አሁን ችግራቸው የሚቀረፍበት ጉዜ ደርሶ ግንባታ በመጀመሩ የተሰማቸው ደስታ ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል።








